የጋሬዝ ክሩክስ ምርጥ ቡድን፡ ፖግባ፣ ባርክሌ፣ ሃዛርድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሳምንቱ ትልቅ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ጨዋታ አንፊልድ ላይ ተደርጎ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ ያለምንም ጎል አቻ ተለያይተዋል።
ትልቅ ድል ያስመዘገቡት በርንማውዝ እና ማንቸስተር ዩናይትድ ናቸው። በርንማውዞች ውጤታማ ጉዞ ላይ የነበሩትን ዋትፎርዶችን ሲያሸንፉ፤ በኒውካስል 2 ለ 0 ሲመሩ የነበሩት ማንቸስትር ዩናይትዶችም ሶስት ነጥብ ለመሰብሰብ ችለዋል።
የትኞቹ ተጫዋቾች በሳምንቱ ምርጥ 11 ቡድን ውስጥ መካተት የሚያስችላቸውን አቋም አሳዩ?
ግብ ጠባቂ - አስሚር ቤጎቪች
አስሚር ቤጎቪች በዋትፎርዱ ተከላካይ ክርስቲያን ካባሴል ጥፋት ተፈጽሞበት ነበር።
ግብ ጠባቂው ከጉዳቱ አገግሞ በርንማውዞች ከሜዳቸው ውጭ ባስመዘገቡት ድንቅ ውጤት ላይ ምንም ጎል እንዳይቆጠርበት በማድረግ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።
ከጥር በኋላ አስሚር ቤጎቪች ከሜዳቸው ውጭ ጎል ሳይቆጠርበት የወጣበት የመጀመሪያው ጨዋታ ነው።
ተከላካዮች - ሄክተር ቤለሪን፣ ኮኖር ኮዲ እና ጆ ጎሜዝ

ሄክተር ቤለሪን፡ የኡናይ ኤምሬ አብዮት እንደቀጠለ ነው። ሜሱት ኦዚል በጉዳት ባይኖርም አርሰናሎች ኳሱን እያንሸራሸሩ ተጫውተዋል።
ከዚህ ጀርባ ያለው ደግሞ ሄክተር ቤለሪን ሲሆን፤ በማጥቃት ላይ ያለው ተሳትፎ እየጨመረ ይገኛል።
ሄክተር ቤለሪን በዘንድሮው የውድድር ዓመት ለጎል የሚሆኑ ሁለት ኳሶችን አቀብሏል። ባለፈው ውድድር ዓመት ሶስት ኳስ ብቻ ነበር ያቀበለው።
ኮኖር ኮዲ፡ ይህ ተጫዋች ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የማይጠራው ለምንድነው? ባለፈው ዓመት ለዎልቭሶች ድንቅ ብቃቱን ያሳየ ሲሆን፤ ቡድኑን ለሻምፒዮን ሺፑ ከማምጣት ባለፈ በፕሪሚየር ሊጉም ውጤታማ መሆኑን እያስመሰከረ ነው።
ከክሪስታል ፓላስ ጋር በነበረው ጨዋታ የዎልቭስ ምርጥ ተጫዋች መሆኑን ለማሳየት ችሏል።
ኮኖር ኮዲ ስድስት ኳሶችን የተከላከለ ሲሆን በዚህ ረገድ ከቡድን አጋሩና ተከላካዩ ዊሊ ቦሊ ጋር እኩል ነው።
ጆ ጎሜዝ፡ አንፊልድ ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ራስን አረጋግቶ ትኩረትን ጨዋታ ላይ ማድረግ አስቸጋሪ ሲሆን ጎሜዝ ይህንን አሳክቷል።
ከሌሎቹ ተከላካዮች በተለየ መልኩ ጎሜዝ አስተማማኝ ነበር። የትኛውም ቦታ ላይ ይሰለፍ ይህንኑ የሚያስመሰክር ተጫዋች ነው።
በሊጉ፤ ጆ ጎሜዝ ከተሰለፈባቸው 25 ጨዋታዎች መካከል ሊቨርፑል ሽንፈት ያስረተናገደው በአንዱ ብቻ ነው።
አማካዮች - ሮዝ ባርክሌ፣ ፖል ፖግባ፣ ሉካስ ቶሪዬራ እና ጊልፍ ሲጉርድሰን

ሮዝ ባርክሌ፡ ወደ እንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን መመለስን እንዴት መግለጽ ይቻላል? ከሳውዝሃምፐትን ጋር በነበረው ጨዋታ ሮዝ ባርክሌ ድንቅ ብቃቱን መልሶ ለማሳየት ችሏል።
ተጫዋቹ ቼልሲ እንዲያሸንፍ ከማገዙም ባለፈ ለቡድኑ የመጀመሪያ ጎሉን አስቆጥሮ ኤደን ሃዛርድ ያስቆጠራትን ኳስም አመቻችቶ አቀብሏል።
ፍራንክ ላምፓርድ እ.አ.አ በ2013 ጎል አስቆጥሮ ለጎል የሚሆን ኳስ ካመቻቸ በኋላ ለቼልሲ ይህን ያደረገው እንግሊዛዊ ሮዝ ባርክሌ ነው።
ፖል ፖግባ፡ ጆሴ ሞውሪንሆ ፖል ፖግባን ይቅርታ ሊጠይቁት ይገባል። ፈረንሳዊው በሁለተኛው አጋማሽ ድንቅ እንቅስቃሴ ነው ያደረገው።
በቡድኑ ውስጥ ያለው ችግር በአብዛኛው የሚመነጨው ከአሰልጣኙ ነው። ፖግባ ደግሞ ቡድኑን ወደ ድል በመመለስ ረገድ ትልቅ ሚና ነበረው። ቡድኑን ከሽንፈት ብቻ ሳይሆን ሞውሪንሆንም ከመባረር አድኗል።
ይህን ያውቃሉ? በሊጉ ፖል ፖግባ በሞውሪኒሆ ቡድን ውስጥ በ29 ጎሎች ላይ ተሳትፎ አለው። ይህ ደግሞ የቡድኑ ቀዳሚ ተጫዋች ያደርገዋል።
ሉካስ ቶሪዬራ: ከፉልሃም ጋር በነበረው ጨዋታ ኡራጋዊው ተጫዋች ጥሩ ሲንቀሳቀስ አምሽቷል።
ቶሪዬራ ቡድኑ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ቢፈጥርም በአርሰናል ደጋፊዎች ዘንድ የፈጠረው ደግሞ ከዚህም የሚልቅ ነው። ምክንያቱም ደጋፊዎቹ ይወዱታል።
ይህን ያውቃሉ? ሉካስ ቶሪዬራ ቋሚ ሆኖ በተሰለፈባቸው ሶስት ጨዋታዎች አርሴናል ሁሉንም ሲያሸንፍ አንድ ጎል ብቻ ነው የተቆጠረበት።
ጊይልፍ ሲጉርደሰን: የሲጉርድሰን 50ኛው የፕሪሚየር ሊግ ጎል ከግብ ክልል ውጭ ያስቆጠረው 19ኛ ጎሉ ሆና ተመዝግባለች። እ.አ.አ ከ2012 በኋላ የሲጉርድሰንን ያህል ከግብ ክልል ውጭ ጎሎችን ያስቆጠረ ተጫዋች የለም።
ተጫዋቹ ሁሌም አስደማሚ ጎሎችን ነው የሚያስቆጥረው። ኤቨርተን በአሰልጣኝ ማርኮ ሲልቫ ስር ጥንካሬ እየተላበሰ ይገኛል።
ጊይልፍ ሲጉርድሰን በፕሪሚየር ሊጉ 50 ጎሎችን በማስቆጠር ከይዱር ጉድዮንሰን በመቀጠል ሁለተኛው አይስላንዳዊ ነው።
አጥቂዎች - ጆሹዋ ኪንግ፣ አሌክሳንደር ላካዜት እና ኤደን ሃርድ

ጆሹዋ ኪንግ: ጆሹዋ ኪንግ ሁለት ጎሎችን ከዋትፎርድ ጋር በነበረው ጨዋታ አስቆጥሯል።
በጨዋታው ክሪስቲያን ካባሳል እና ዋትፎርድ ለጥፋታቸው ቅጣቱን አግኝተዋል።
የበርንማውዙ ጆሹዋ ኪንግ 34 ጎሎችን በሊጉ ያስቆጠረ ሲሆን ከእሱ በላይ ያስቆጠሩ ኖርዌያዊያን አራት ብቻ ናቸው።
አሌክሳንደር ላካዜት፡ አጥቂው ድንቅ ብቃት ላይ ከመሆኑም በላይ አስገራሚ ጎሎችን እያስቆጠረ ነው። ጎሎችን በቀላሉ በማስቆጠር ላይ ይገኛል።
በሳምንታት ውስጥ ምን ያህል ለውጥ ተመዘገበ? ላካዜት ከሳምንታት በፊት ለአርሰናል በቋሚ ካለመሰለፉም በላይ በክለቡ ያለው ቆይታ ላይ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር። እነዚህ ጥያቄዎች አሁን አይነሱም።
በዘንድሮው ዓመት የሊግ ጨዋታዎች በአምስት ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት በመሰለፍ በስድስት ጎሎች ላይ በቀጥታ ተሳትፏል።
ኤደን ሃዛርድ፡ ከሳውዝሃምፕተን ጋር በነበረው ጨዋታ ኤደን ሃዛርድ በድጋሚ ችሎታውን ለማሳየት ችሏል። አሁን ባለው አቋም ያለምንም ጥርጥር የፕሪሚየር ሊጉም ሆነ የአውሮፓ ምርጥ ተጫዋች ነው።
አሁን ያለው ብቸኛው ችግር ቼልሲዎች ተጫዋቹን በጉዳት ካጡት ነው። ቡድኑ ከሚገባው በላይ በእሱ ላይ ጥገኛ የሆነ ይመስላል።
ከሁለት ዓመት ወዲህ ኤደን ሃዛርድ በሊጉ ጎል አስቆትሮ ለጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።
































