በየመን ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ በአንድ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት ተፈጸመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በየመን ደቡባዊ ጠረፍ አካባቢ በአንድ ጀልባ ላይ የተሳፈሩ ታጣቂዎች በጭነት መርከብ ላይ ተኩስ ከፍተው ጥቃት መፈጸማቸውን የዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ደኅንነት ተቋም አስታወቀ።
የዩኬ የባሕር ትራንስፖርት ኦፕሬሽን የተባለው ተቋም እንዳለው፣ በንግድ መርከቡ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው ከየመን የሙካላ የባሕር ጠረፍ ደቡብ ምዕራብ ላይ ነው።
በዓለም አቀፍ የመርከብ መተላለፊያ በኩል ወደ ምሥራቅ በማቅናት ላይ የነበረው የጭነት መርከብ፣ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎችን ከተሳፈሩበት ትንሽ ጀልባ ተኩስ ተከፍቶበት የመርከቡ ጠባቂዎች የማስጠንቀቂያ መልስ መተኮሳቸውን ተቋሙ ገልጿል።
ከመርከቡ የታጠቁ ጠባቂዎች በተከፈተባቸው የአጸፋ ተኩስ ምክንያት አጥቂዎቹን ያያዘው ትንሽ ጀልባ ከቦታው ለመራቅ በመገደዱ የጭነት መርከቡ ጉዞውን መቀጠሉን ኤጀንሲው አመልክቷል።
የመርከቡ ካፒቴን በመርከቡ ላይ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰ እና ከሠራተኞቹም መካከል የተጎዳ እንደሌለ ሪፖርት አድርጓል።
የመርከብ እንቅስቃሴዎችን የሚከታተለው ኤጀንሲ ጥቃቱ የተፈጸመበት የጭነት መርከብ፣ በየትኛው አገር እንደተመዘገበ እና እያንቀሳቀሰው ያለው ተቋም ማን እንደሆነ እንዲሁም ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ አልገለጸም።
ይህ ጥቃት ባለፈው ማክሰኞ ዕለት በየመን ጠረፍ አካባቢ በአንድ ሌላ የጭነት መርከብ ላይ ከተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት በኋላ ያጋጠመ ነው።
በየመን እና በሶማሊያ ባለው አለመረጋጋት ምክንያት በሕንድ ውቅያኖስ እና በቀይ ባሕር ደቡባዊ ክፍል ላይ በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተደጋገሙ መጥተዋል።








