አሜሪካ፡ ንጉሳዊ ቤተሰብ ነኝ በማለት ያጭበረበረችው ጥፋተኛ ተባለች

የፎቶው ባለመብት, BFA
አና ሶሮኪን የአሜሪካዋ ኒውዮርክ ከተማ ሃብታሞችን ቀልብ ለመሳብ ብዙም አልፈጀባትም። የቢሊየን ዶላሮች ባለቤትና የጀርመን ንጉሳዊ ቤተሰቦች አባል ነኝ በማለት በሄደችባቸው ግብዣዎች ሁሉ ብዙ ሺ ዶላሮችን ለሰዎች መስጠት ልማዷ ነበር።
የግል አውሮፕላን ተከራይታ ስትንቀሳቀስና ለሹፌሮቿ እንዲሁም ቦርሳዋን ለያዘላት ሰው ጭምር ብዙ ዶላሮች ስታበረክት 'እንዴት ያለች ሃብታም ንጉሳዊ ቤተሰብ ናት' በማለት ብዙዎች እሷን ጓደኛቸው ለማድረግ ተሯሩጠዋል።
ነገር ግን ይሄ ሁሉ ታዋቂነትና ተወዳጅነት ብዙ አልቆየም።
እውነታውም ሌላ መሆኑ ተሰምቷል። እሷ እንደምትለው በራሷም ሆነ በቤተሰቧ ስም ቢሊየን ዶላር የለም። አባቷም የቀድሞ ከባድ ተሽከርካሪ ሹፌር ሲሆኑ በአሁኑ ሰአት በግል የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
ይህ መረጃ የደረሳቸውና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ገንዘብ እንዲከፍሏት ያስገደደቻቸው ሰዎች ጉዳዩን ወደ ፖሊስ ለመውሰድ ብዙ ጊዜም አልፈጀባቸውም።
አንድ ወር በፈጀው የፍርድ ሥነ ሥርዓት አና ሶሮኪን በብዙ የማጭበርበር ክሶች ጥፋተኛ የተባለች ሲሆን ከ200 ሺ ዶላር በላይ አጭበርብራለች የሚል ክስም ቀርቦባታል።
የፍርድ ቤት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሶሮኪን 60 ሚሊየን ዶላር የሚገመት ንብረት ያላት የጀርመን ንጉሳዊ ቤተሰብ በመምሰል 20 ሚሊየን ዶላር ከባንክ ለመበደር ጥያቄ አቅርባ ነበር።
ምንም እንኳን ጥያቄዋ ተቀባይነት ባያገኝም 'ሲቲ ናሽናል' ከተባለው ባንክ 100 ሺ ዶላር ብድር አግኝታለች።
ከዚህ በተጨማሪም እስከ 55 ሺ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ አልባሳት ላይ ብታውልም እስካሁን ከፍላ አልጨረሰችም። ያረፈችበት ሆቴልም ቢሆን "ተገቢው ክፍያ አልተሰጠኝም፤ የግል አካላዊ እንቅስቃሴ አሰልጣኝ ቀጥራም ነበር፤ እሱም ቢሆን ክፍያ አልተፈጸመበትም" ብሏል።
ሶሮኪን እስካሁን ድረስ ድርጊቱን ክዳ እየተከራከረች ቢሆንም እስከ 15 ዓመት የሚደርስ እስር እንደሚፈረድባት ይጠበቃል። የመጨረሻ የፍርድ ሂደቱም በመጪው ወር የሚካሄድ ይሆናል።
































