ቢቢሲ የ2022 የኮምላ ዱሞር ውድድርን ይፋ አደረገ

ኮምላ ዱሞር
ታትሟል

ቢቢሲ በአፍሪካ የጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ጎልተው የሚወጡ ኮከብ ጋዜጠኞችን "በቢቢሲ ወርልድ ኒውስ የኮምላ ዱሞር ሽልማት" አማካኝነት ለሰባተኛ ጊዜ አመልካቾችን መቀበል ጀመረ።

አዲስ ተሰጥኦን አጉልቶ በሚያወጣው ውድድር ላይ ጋዜጠኞች ከመላው አፍሪካ ለዚህ ሽልማት እንዲያመለክቱ ተጋብዘዋል።

በዚህ ውድድር አሸናፊ የሚሆን ጋዜጠኛ ለንደን በሚገኘው የቢቢሲ ዋና መስሪያ ቤት ለሦስት ወራት በመቆየት ልምድና ክህሎትን ለማዳበር እድል ይሰጣል።

የውድድሩ የማመልከቻ ጊዜ የሚያበቃው የካቲት 9 2014 ዓ.ም. ነው።

ይህ ሽልማት የተጀመረው ከዓመታት በፊት በ41 ዓመቱ በድንገት ህይወቱ ያለፈውን ባለድንቅ ተሰጥኦ ባለቤት ጋናዊ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ኮምላ ዱሞርን ለማስታወስ ነው።

የኮምላ ዱሞር ባለቤት ክዋንሴማ ዱሞር ባለቤቷ በቢቢሲ ጥሎት ያለፈው መልካም ስም እንደሚያኮራት እና ቢቢሲም በቀድሞ ጋዜጠኛው ስም ይህን ሽልማት ማዘጋጀቱ ምስጋናዋን አቅርባለች።

ቢቢሲ በአፍሪካ የሚኖሩ እና የሚሰሩ ጠንከራ የጋዜጠኝነት ክህሎት ላላቸው ጋዜጠኞች ሽልማቱን ይሰጣል።

ይህን ውድድር የምታሸንፈው/የሚያሸንፈው ጋዜጠኛ ለንደን ውስጥ በቢቢሲ ዋና መስሪያ ቤት ከምታገኘው/ከሚያገኘው ስልጠናዎች በተጨማሪ አፍሪካ ውስጥ ወደሚገኝ አገር በመጓዝ ዘገባዎችን እንዲሰሩ ዕድሉን ያገኛሉ።

line

የቀደሙ ዓመታት የኮምላ ዱሞር ውድድር አሸናፊዎች:

  • 2015: ናይሲ ካኩንጊራ ከኡጋንዳ
  • 2016: ዲዲ አኪንዬሉር ከናይጄር
  • 2017: አሚና ዩጉዳ ከናይጄሪያ
  • 2018: ዋይሂጋ ምዉራ ከኬንያ
  • 2019፡ ሶሎሞን ሴራዋንጃ ከኡጋንዳ
  • 2020፡ ቪክቶሪያ ሩባዲሪ ከኬንያ

በ2020 የኮምላ ዱሞር አሸናፊ የሆነችው ኬንያዊቷ ቪክቶሪያ ሩባዲሪ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ልምምዷን ማካሄድ ባለመቻሉ ወደ 2021 ተሸጋግሮላታል።

ቪክቶሪያ በቢቢሲ ቆይታዋ ወደ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ መዲና ኬንሻሳ ተጉዛ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ደህንነት ለማሻሻል ተግባር ላይ ስለዋለው መተግበሪያ ዘገባ ሰርታለች።

በአውሮፓውያኑ 2007 ላይ ቢቢሲን የተቀላቀለው ኮምላ፤ እስከ ድንገተኛ ህልፈቱ ድረስ በተለያዩ ኃላፊነቶች በቢቢሲ በጋዜጠኝነት አገልግሏል።

በርካቶች ኮምላ ዱሞርን የሚያውቁት በቢቢሲ ዎርልድ ኒውስ ላይ የሚተላለፈውን ፎከስ ኦን አፍሪካ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ሆኖ ነው።

ኮምላ ቢቢሲ ዎርልድ ሰርቪስ ላይ የሚተላለፈውን ኔትዎርክ አፍሪካ እንዲሁም ዘ ዎርልድ ቱዴይ ፕሮግራሞችን መርቷል።

ኮምላ በአውሮፓውያኑ 2013 ላይ የኒው አፍሪካ መጽሄት 100 ተጽእኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን ዝርዝር ውስጥ መካተት ችሎ ነበር።