የ85 ዓመቱ የካሜሩን ፕሬዝዳንት ለሰባተኛ ጊዜ ምርጫ ማሸነፋቸውን የተመለከቱና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

የፎቶው ባለመብት, ANADOLU AGENCY/ GETTY IMAGES
ኢትዮጵያ
• በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ከአንድ የ33 ዓመት ወጣት ሆድ ውስጥ 120 ሚስማሮች፣ አንድ መርፌ ቁልፍ፣ ሁለት መርፌ፣ ሁለት ስቴኪኒና ሁለት ስባሪ ብርጭቆዎች በቀዶ ህክምና መውጣታቸውን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
ለብዙ ዓመታት የአዕምሮ ህመምተኛ የነበረው ወጣት ለስምንት ዓመታት ህክምና ሲከታተል እንደቆየ ተገልጿል።
• ወደ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ካማሺ ዞን ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ መግባታቸውን የክልሉ መንግስት ማስታወቁን ዶቼ ቤሌ ዘገበ።
እርዳታው በካማሺ ዞን ውስጥ ላሉ "57 ሺህ 625 እርዳታ ፈላጊዎች እንደሚከፋፈል የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም ጃለታ ተናግረዋል።
ናይጄሪያ
• ከአንድ ዓመት በላይ ጠፍቶ የነበረው ናይጄሪያዊ የአማጺ ቡድን መሪ ናምዲ ካኑ እስራኤል ውስጥ እንደሚገኝ አስታወቀ።
ሰውዬው በደቡብ ምስራቃዊ ናይጄሪያ የምትገኘውን ቢያፍራ ግዛት ራሷን የቻለች ሃገር እንደትሆን ሲቀሰቅስ ነበር።
ኒጀር
• በኒጀር ደቡባዊና ማዕከላዊ ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች የሚጠጡት ውሃ ውስጥ በተገኘ ከፍተኛ መጠን ያለው የፍሎራይድ ክምችት ምክንያት ከመንግስት ካሳ ሊያገኙ ነው።
ከአምስት ሺ በላይ ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ መንግስት እስከ 3.5 ሚሊዯን ዶላር ድረስ ሊከፈል እንደሚችል ተገልጿል።
ካሜሩን
• የ85 ዓመቱ የካሜሩን ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ ለሰባተኛ ጊዜ ሃገራቸውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን አሸነፉ።
ተፎካካሪያቸው ሞሪስ ካምቶ ምርጫው የተጭበረበረ ነው እንደገና መካሄድ አበት ብለዋል።
ህንድ
•ባለፈው አርብ ህንድ ውስጥ የተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ተገለብጦ ከ60 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የባቡር አደጋ ጋር በተያያዘ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ።
ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለመበተን ዱላ የተጠቀመ ሲሆን፤ እስካሁን ያልተገኙ ሰዎች ቁርጥ ይነገረን በማለት ነው ወደ መንገድ የወጡት።
ሆንግ ኮንግ
• 55 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የዓለማችን ረጅሙ የባህር ላይ ድልድይ ሆንግ ኮንግ ውስጥ ሊመረቅ ነው።
የድልድዩ መሰረት ወደ ታች 6.7 ኪሎሜትር የሚረዝም ሲሆን፤ የመሬት መንቀጥቀጥና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች መቋቋም ይችላል።
ፓስፊክ
• በደቡባዊ ፓስፊክ የሚገኙ ትላልቅ አይጦች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የባህር አእዋፍ ልጆችን እየገደሉ እንደሆነ ተገለጸ።
አይጦቹ ያልተፈለፈሉ እንቁላሎችንና ታዳጊዎቹን ስለሚበሏቸው አእዋፎቹ የመጥፋት አደጋ ተጋርⶏባቸዋል።
ሳኡዲ አረቢያ
• ሳኢዲ አረቢያ ታዋቂው ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጂ ቱርክ በሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤት ውስጥ መገደሉን አመነች።
ሳዑዲ ጀማል መገደሉን ከማመኗ በፊት በቆንስላው ውስጥ በነበሩ ሰዎች እና ጀማል መካከል በተፈጠረ ጸብ ምክንያት ሊሞት ችሏል ብላ ነበር።
አሜሪካ
• በአሜሪካ ኢንዲያናፖሊስ በሚገኝ የእንስሳት ማቆያ ውስጥ የምትኖር አንዲት አንበሳ የሶስት ልጆቿን አባት ገደለች።
ባልተለመደ መልኩ ማጓራት የሰሙት የመካነ አራዊቱ ሰራተኞች በቦታው ሲደርሱ አንበሳዋ የአጋሯን አንገት ጨምድዳ ይዛ እንደነበረ ተናግረዋል።





























