ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና እና 'አሻሚ' ቃላታቸው

የፎቶው ባለመብት, YONAS TADESSE
የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር ከተረከቡ 100 ቀናት ሊሆናቸው ጥቂት የቀራቸው አብይ አሕመድ ብዙዎች ያልገመቷቸው ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አከናውነዋል።
በፖለቲካ ምክንያት የታሠሩ ሰዎችን ከመፍታት አንስቶ በሽብርተኝነት ጥቁር መዝገብ ላይ የሠፈሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ከመዝገቡ እስከ መፋቅ ያሉ ለውጦች መታየት የጀመሩት በአሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዘመን ነው።
በርካቶች እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ከግምት ወስጥ በማስገባት ጉዳዩ 'የመንግሥት ለውጥ' ይመስል ይዟል ሲሉ ግላዊ አስተያየታቸውን መስጠት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ እርምጃዎች ጎን ነን ያሉ ቁጥራቸው ላቅ ያለ ኢትዮጵያዊያንም አደባባይ በመውጣት ድጋፋቸውን ማሰመት ከጀመሩ እነሆ ቀናት አልፈዋል።
በማሕበራዊ የመገናኛ ዘዴዎችም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የተመለከቱ ዜናዎችና ሃተታዎችን ሳይመለከቱ ማለፍ ዘበት ሆኗል።
አንድነትን በሚያበረቱ ንግግሮቻቸው የሚታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ተገኝተው የሚሰጧቸው አንዳንድ አስተያየቶች ግን በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እያገኙ አይደሉም።
አሻሚ ቃላት
ከሳምንታት በፊት 'የቀን ጅብ' የሚል ቃል ተጠቅመዋል በሚል ትችት የተከተላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑም አንድ አጨቃጫቂ ቃል ወጥቷቸዋል፤ 'ፀጉረ ልውጥ' የሚል።
ለመብት ሙግት በመግጠም የሚታወቀው የዞን 9 ጦማሪው በፍቃዱ ኃይሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍ በሚወጡ ቃላት የተስማማ አይመስልም።
«አገላለፆቹ ተምሳሌታዊ ከመሆናቸው አንፃር ለቃላት ውበት ጠቀሜታ ሊኖራቸው ይችላል። ነገር ግን ከአንድ ሃገር መሪ ሲመጡ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ቀለል ተደርጎ ሊታይ የሚገባው አይደለም» ይላል።
ለበፍቃድ ትልቁ ስጋት ቃላቱ አሻሚ በመሆናቸው የሚመደቡበት ሥፍራ ግልፅ አለመሆኑ ነው። «ሰዎች እኚህን ቃላት ከፈለጉት ማሕበረሰብ ጋር በማገናኘት የራሳቸው የሆነ ትርጉም ይሰጧቸዋል» ሲል ያሰምራል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ መምህርና እና በቅርቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ በአዲስ አበባ የተደረገውን ሰልፍ ካስተባበሩት መካከል አንዱ የነበረው አቶ ስዩም ተሾመ ከበፍቃዱ ተቃራኒ የሚቆም ሃሳብ አለው።
«ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃላቶቹን የተጠቀሟቸው በአውድ በአውዱ ነው፤ አስፈላጊ ነው ባሉበት ሁኔታ ነው የተጠቀሟቸው» ሲል ይከራከራል።
«ሚሊዮን ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦንብ የሚወርውሩ ሰዎች እንዲህ ሊገሰፁ ይገባል፤ እንደውም የሚገባቸውን ያህል ግሳፄ አግኝተዋል ብዬ አላስብም» ይላል አቶ ስዩም።
እንደ አቶ ስዩም ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የገሰፅዋቸውን ሰዎች ሕብረተሰቡ ንቁ ሆኖ መጠበቅ አለበት።
«ዜጎችን እርስ በርስ እያባሉ የሥልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም ከሚሯሯጡ ሰዎች ጎንስ መቆም አግባብ ነው ወይ?» ሲል ይጠይቃል አቶ ስዩም።
ለበፍቃዱ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቃላት አጠቃቀም አደጋ ያነገበ ነው፤ ዋነኛው አደጋ ደግሞ ሰዎች እነኚህን ቃላት ሌሎችን ለመውቀስ እየተጠቀሙባቸው መሆኑ ነው።
«ሲቀጥል...» ይላል በፍቃዱ «ሲቀጥል የፈለገ ስጋት ቢኖር የሕግ አካላት እርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ እንጂ ሕብረተሰቡ ይህንን እንዲያደርግ መጠየቅ ተገቢ አይደለም።»
«ምንም እንኳ መሰል ለውጦች ሲመጡ የማይዋጥላቸውና ለለውጡ ዝግጁ ያልሆኑ ሰዎች ቢኖሩም እንዲህ ዓይነት አሻሚ ቃላት መጠቀም ግን መፍትሄ ነው ብዬ አላስብም» ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
«አዲስ ነገር አይደለም»
«እርግጥ ነው ከዚህ በፊት ባሉት አመራሮችም ሆነ መንግሥታት ቃላትን ተጠቅሞ አንድን ቡድን ወይም ግለሰቦችን የመፈረጅ አዝማሚያ የተለመደ ነው» ይላሉ የሥነ-ልሳን ምሁር ዶ/ር ጊደና መስፍን።
በደርግ ዘመን 'የፍየል ወጠጤ' የተሰኘ ቃል ጥቅም ላይ ይውል እንደነበረ የሚያስታውሱት ምሁሩ በዘመነ ኢህአዴግም ቢሆን ከ'አደገኛ ቦዘኔ' ጀምሮ እስከ 'ኪራይ ሰብሳቢ' ድረስ በርካታ ቃላት ጥቅም ላይ እንደዋሉ ያወሳሉ።
ምሁሩ ጉዳዩ አዲስ ነገር እንዳልሆነ ቢያሰምሩም ቅሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊያስተላልፉ የፈለጉትን መልዕክት እንዳይሸፍንባቸው ይሰጋሉ።
«ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትን እንዲሁም ኢትዮጵያዊነትን ነው እየሰበኩ ያሉት። ይህን ተከትሎም የህዝቡን ቀልብ መግዛት ችለዋል።»
«ግን አልፎ አልፎ በሙያው vague metaphor (አሻሚ የሆነ ምሳሌ) የምንላቸውን ቃላት ይጠቀማሉ። እኔ የምሰጋው ሰው እኒህን አሻሚ ቃላት ከአውድ ውጭ እንዳይወስዳቸው ነው» ይላሉ።
ለምሁሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠቀሟቸው ቃላት አቅደውም ሆነ እንዲሁ በጎ መልዕክት ለማስተላለፍ እንኳ ቢሆን፤ በተቀባዩ ዘንድ የሚኖራቸው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
«አንዳንድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠቀሟቸው ቃላትን ሰዎች ባነር አሰርተው ሰልፈ ሲወጡ ተመልክተናል። ይህ ቃላት ምን ያህል ኃይል እንዳላቸው ያስገነዝበናል።»
እነማን ናቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 100 ቀናቸውን እየደፈኑ ነው። በእነዚህ ጊዜያት ታድያ አንድነትን የሚያድሱ እና ሰላምን የሚሰብኩ ንግግሮቻቸው ከብዙዎች ዘንድ ደርሰዋል።
ነገር ግን አነጋጋሪነት ያልተለይዋቸው ንግግሮች ወይም ሃረጋት በተለያዩ ሰዎች በኩል የተለያየ ግንዛቤ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል የሚሉ ሰዎች አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሻሚ ቃላትን መጠቀም የለባቸውም ብሎ በሚከራከረው በፍቃዱና መሰል ቃላትን መጠቀም ጉዳት የለውም ብሎ በሚያምነው ስዩም መካከል ያለው አጣማሪ መስመር፤ የሰውየውን ለውጥ የማይሹ ኃይሎች አሉ የሚለው ነው።
ግን እኚህ ኃይሎች እነማን ናቸው?
ለምሁሩም ሆነ ለበፍቃዱ ትልቁ ጥያቄ ይሄ ነው። «ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንን ነው መናገር የፈለጉት ተብዬ ብጠየቅ ቁርጥ ያለ ምላሽ ልሰጥ አልችልም፤ የዚህ ጥያቄ ምላሽ ያለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ብቻ ነው።»
«መሰል አሻሚ ቃላት ሰው እንደፈለገው እንዲተረጉመውና ለፈለገው ዓላማ እንዲያውለው መንገድ ያበጁለታል። ውጤቱም አሉታዊ ሊሆን ይችላል።» እንደ ዶ/ር ጊዴና ገለፃ አሁን ላይ ሃገሪቱ ውስጥ ያለውን አዎንታዊ የሆነ ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ስሜታዊነት ይነበባል።
«እርግጥ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅርን በመስበክ አይታሙም፤ ቢሆንም አሻሚ ቃላት ያላቸው አሉታዊ ተፅዕኖ የሚናቅ አይደለምና ቢያስቡበት» ሲሉ ምሁሩ ምክር ጣል ያደርጋሉ።





























