በናይጄሪያ በአርብቶ አደሮችና በአርሶ አደሮች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት 86 ሰዎች ሞቱ

ፉላኒዎቹ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ውሃ ሲያጠጡ
ታትሟል

በማዕከላዊ ናይጄሪያ በአርሶ አደሮችና በአርብቶ አደሮች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 86 ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ግጭቱ ሐሙስ ዕለት አርሶ አደሮቹ የቤሮም ጎሳ አባላት አርብቶ አደሮቹን የፉላኒ ጎሳ አባላትን ካጠቁና 5 ሰዎች ከሞቱ በኋላ እንደተቀሰቀሰ ለማወቅ ተችሏል።

ቅዳሜ ዕለት የወሰዱት የበቀል እርምጃም ለበርካቶች ሞት መንስኤ ሆኗል።

በአካባቢው የሚኖሩ ብሔረሰቦች በመሬት የተነሳ በተደጋጋሚ ይጋጫሉ።

በግዛቲቱ ሦስት አካባቢዎች የሰዓት እላፊ ታውጇል።

የሀገሪቱ ፖሊስ ኮሚሽነር የሆኑት አንዲ አዴ እንዳሉት በግጭቱ 86 ሰዎች እንደሞቱ እና ሌሎች 6 ሰዎች እንደተጎዱ ከተገለፀ በኋላ ወንጀለኞችን ለማደን መንደሮችን የማሰስ ሥራ ተጀምሯል።

ኮሚሽነሩ አክለውም 50 ቤቶች፣ 15 ሞተር ሳይክሎች እና 2 መኪኖችም መቃጠላቸውን አስታውቀዋል።

የፕላቱ ግዛት አስተዳዳሪ እንደገለፀው ሕግና ሥርዓትን ግጭቱ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ለማስፈን እንዲቻል የሰዓት እላፊው ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ ፀንቶ ይቆያል።

በማዕከላዊ ናይጄሪያ በአርብቶ አደሮችና በአርሶ አደሮች መካከል በግጦሽ መሬት የተነሳ ግጭቶች የተለመዱ ናቸው።

ይህ በጎሳዎች መካከል የሚደረግ የበቀል ግድያ ባለፈው ዓመት ብቻ በሺዎች ለሚቆጠሩ ግለሰቦች ሕይወት መጥፋት ሰበብ ሆኗል።